“ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት” ከሚለው የንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደየሱስ መጽሐፍ የተወሰደ
ከከበረ ሰላምታ ጋር…
“የኅዳር ሚካኤል” ተብሎ በኅዳር ፲፪ ቀን የሚከበረው የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በዓል ነው።
እግዚአብሔር፡ የእሥራኤልን ሕዝብ በሙሴ አማካይነት ከፈርዖን የባርነት አገዛዝና ከምድረ ግብፅ የሥቃይ ኑሮ ነጻ አውጥቶ መዓልቱን በደመና ሌሊቱንም በእሳት ዓምድ ከልሎ እየመራቸው የቀይ ባሕርንም በደረቅ ምድር አሻግሮ እየጠበቃቸው፡ ውኃውን ከዓለት አፍልቆ ኅብስተ መናውን ከሰማይ አውርዶ፡ “ሥጋ አማረን” ቢሉም ድርጭቱን በነፋስ አዝንሞ እየመገባቸው እንደተንከባከባቸው ይታወቃል፡ በአምላካቸው ቸርነት ይደረግላቸው የነበረውን ያን ኹሉ የተራዳዒነት ተልእኮ ይፈጽምላቸው የነበረው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነበር። ይኹን እንጂ እነርሱ ለዚህ ኹሉ አምላካዊ ቸርነት ውለታቢሶች በመኾን ፈጣሪያቸውን አሳዘኑ፡ ይኸውም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ወደተራራ ወጥቶ ለጥቂት ቀናት በሱባዔ መቆየቱን ምክንያት አድርገው፡ ካህን ወንድሙን አሮንን “በፊታችን የምናስቀድመው ጣዖት ካልሠራህልን” ብለው አስጨንቀው ጣዖቱን ማሠራታቸውና ማምለካቸው ነው።
እነርሱ ሊጠፉበት የነበረውን የእግዚአብሔርን ቍጣ፡ ሙሴ በማለሟልነቱ አማልዶ ቢያስመልሳቸውም የእነርሱ ማለትም የእሥራኤል ልጆች ፍላጎት፡ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች፡ እግዚአብሔርን በእውነትና በመንፈስ ማምለክ ሳይኾን እንደአሕዛብ በሚታይና በሚዳሰስ ግዙፍ ነገር መኾኑን እግዚአብሔር ተመለከተ፡ እንዲህ ከኾነ ብሎም እርሱ እግዚአብሔር ቃሉን በጽላት ላይ ቀርፆ ያንም ጽላት በግእዝ “ታቦት” በሚባለው ሣጥን ውስጥ እንዲያስቀምጡት አዝዞ፡ በዚያ እንዲያመልኩት “ታቦተ ጽዮን” የተባለችውን ያቃል ኪዳን ምስክር ሰጣቸው። ከዚህ የተነሣ ጠላቶቻቸውን ድል ይነሡባት ዘንድ እንዲህ አድርጎ በሰጣቸው እርሱ ለእነርሱ በሚገልጽባት እነርሱም እርሱን በሚያመልኩባት በዚችው የጽላት ሕግ ሃይማኖትና ምግባር ጸንተው ይኼዱ ወይም አይኼዱ እንደኾነ ሊፈትናቸው አርባ ዓመታት ሙሉ በምድረ በዳ አንከራተታቸው። በዚያን ጊዜ ለእሥራኤል ሕዝብ “አንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለኾንህ፡ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ እኔ በአንተ መካከል አልወጣምና በፊትህ መልአኬን እሰድዳለሁ!” ብሎ የመደበላቸው መልአክ፡ ቅዱስ ሚካኤል ነበረ። ይህ ኹሉ ዝክረ ነገር በኦሪት ዘጸአት መጽሓፍ ውስጥ ተመዝግቦ፡ ዛሬ ድረስ እንደሚነበብ ታውቃላችሁ።
በዚያን ዘመን እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ለአብርሃም ለይስሓቅና ለያዕቆብ የገባውን ቃል ኪዳን በማሰብ ለእሥራኤል ልጆች ያን የመሰለ ታዳጊነቱን በመልአኩ በቅዱስ ሚካኤል አገልጋይነት ያደርግ እንደነበረ፡ ዛሬ “እውነተኞቹ እሥራኤል እኛ ስለኾንን ይህንኑ ተራዳኢነቱን ይፈጽምልናል!” ብለው የኢትዮጵያ ልጆች የቅዱስ ሚካኤልን በዓል፡ በዚህ ዕለት ያከብራሉ።
በአገራችን በኢትዮጵያ በዚሁ በኅዳር ሚካኤል ዕለት ካህናቱ በየቤተ ክርስቲያኑ ጸሎተ ዕጣን እየደገሙ የማዕጠንት ዕጣን የሚያሳርጉት ሕዝቡ በከተማ ቍሻሻ የኾነውን ነገር ኹሉ እየሰበሰበ የሚያቃጥለው በገጠርም በየእርሻው በተለይም በቆላ የሚኖረው ወገን ስለወባና ወረርሽኝ በየመሬቱ ላይ እሳት አንድዶ ጪስ የሚያጨሰው “ኅዳር ታጠነ” የሚባለውን ይትበሃል ለማስታወስ ነው፡ የዚህም ምክንያት በራእየ ዮሓንስ ተጽፎ እንደሚነበበው፡ “ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ” የሚባሉት መላእክት ስለዓለሙ ኹሉ ደኅንነት በሰማይ በጽርሐ አርያም የምስጋናና የልመና ጸሎትን ከዕጣን ማዕጠንት ጋር በእግዚአብሔር መንበር ፊት ያለማቋረጥ የሚያቀርቡትን ሥርዓት የተከተለ ነው፡ እንደዚሁ ኹሉ እኛንም እግዚአብሔር በምድር ላይ ካለፈው ዓመት ከማናቸውም ዓይነት ሕማምና ደዌ፡ ቸነፈርና በሽታ ጠብቆ ስላዳነን፡ ከሚመጣውም እንዲጠብቀን በማለት በዚያ ሰማያዊ ሥርዓት እኛም፡ ኢትዮጵያውያን ለፈጣሪያችን ምስጋናችንንና ልመናችንን ይኸው እናቀርባለን፡ በቅርቡ፡ በአጼ ምኒሊክ ዘመን ደርሶ የነበረውን፡ “የኅዳር በሽታ” የሚባለውን ከመሰለ በዓመቱ ውስጥ ተላላፊ የሰውና የከብት በሽታ ገብቶ፡ ሊያደርስ ከሚችለው ጥፋትና ዕልቂት “አድነን” ለማለት።
በዛሬው በኅዳር ፲፪ ዕለት፡ ፪ሺ፯ ዓ.ም፡ ፲፫ ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ህጻናት የልጅነት ልምሻ / ፖሊዮ ተላላፊ በሽታ መከላከያ ክትባት ይሰጣቸዋል። የዜናው ምንጭ አናዱሉ የተባለው የቱርክ የዜና ወኪል መሆኑ የሚገርም ነው። ይህችን ዕለት እናስታውስ! ኹሉን የሚያይ ቸሩ እግዚአብሔር ወገኖቻችንን / ልጆቻችንን ይጠብቅልን!