Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

  • September 2014
    M T W T F S S
    1234567
    891011121314
    15161718192021
    22232425262728
    2930  
  • Archives

  • Categories

  • Recent Posts

ብሩክ የመስቀል በዓል

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on September 25, 2014

ChristosMeskel

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትከሚለው መጽሐፍ የተወሰድ

የመስቀል በዓል በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ ለምን ይከበራል?

ነገር ከሥሩ፥ ውኃ ከጥሩ!” እንደሚባለው፡ ስለመስቀል ታሪክ ሲወሳ አዳምንና ሔዋንን በሚመለከት ከዚህ የሚከተሉት ቍም ነገሮች ይጠቀሳሉ፤ ይኽውም እኒህ ሁለት የመጀሪያ ሰዎች፦

፩ኛ፦ የአምላክ ልጆች ኾነው በቅንነት እንዲመሩበትና ለዘለዓለም ሕያዋን ሆነው በገነት ተድላ እንዲኖሩበት ከፈጣሪያቸው ከተሰጣቸው የእውነት ቃልና ከተጎናጸፉት መልካም ሕይወት ይልቅ፡ ዲያብሎስ ከተባለው የሓሰት አበጋዝ የቀረበላቸውን የጥፋት ምክር በራሳቸው ምርጫ ተቀብለው በክፋት ዓለም መኖርን መምረጣቸው፥

፪ኛ፦ ቆይተው ግን፡ ከዚህ የኃጢአት ምግባራቸው ፍጹም ተጸጽተው ንስሓ በመግባት የፈጣሪያቸውን ምሕረት መጠየቃቸው፥ እግዚአብሔርም ሊነገር በማይቻል ቸርነቱ ኃጢአታቸውን ይቅር ማለቱ፥

፫ኛ፦ እግዚአብሔር የዚህ ይቅርታቸው መገለጫ በሆነው በአንድ ልጁ፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት እነርሱንና የእነርሱን ፈለግ የተከተልን እኛን ዘሮቻቸውን በፈቃዳችን ካመጣነው ከዚያ የፍዳ አገዛዝ የኃጢአት ቀንበርና የሞት ዕዳ ካዳነን በኋላ ጥንቱኑ አዘጋጅቶልን ወደነበረው ወደዘለዓለም መንግሥቱ ሕይወት የመለሰን መሆኑ ከሁሉ በፊት መነሻና መሠረት ሆኖ መነገር አለበት።

ይህም ሁሉ ሊሆን የቻለው፡ አዎን! በቀላል አልነበረም፡ እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም በፍጹም ሰውነት ተወልዶ ያለኃጢአት እውነተኛውን ሰብአዊ ሥርዓት በመኖር ለፍጥረቱ በጎ አርአያ ሆኖ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምንነት በትምህርት ገልጦና አምላክነቱ ንም በተአምራት አሳይቶ ልዩ ልዩ ፈተናዎችን አሸንፎና መከራዎችን ተቀብሎ በመስቀል ላይ ራቁቱን ተሰቅሎና ደሙን አፍስሶ ሙቶና ተቀብሮ በመጨረሻ በትንሣኤው ያን ጨንቀኛ ጠላታቸውን ዲያብሎስን ድል በመንሣት ነው።

ከዚህ ጋር በማያያዝ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ! መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ! ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፉታል! ስለእኒእ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል!” የሚለው የመስቀሉ ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እና የእርሱ ተከታይ ሓዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፡ በመንፈስ ቅዱስ ተመልቶ፡ የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉ ሞኝነት፡ ለእኛ ለምንድን ግን፡ የእግዚአብሔር ኃይል ነው!” በሚል የመክፈቻ አርእስት ስለመስቀል ምስጢር የሰጠው የትርጓሜ ሓተታ አብሮ ሊነገር ይገባል።

የትርጓሜው ሓተታ እንዲህ ነው፦ የአይሁድ ሊቃናት ከካህናቱና ከሕዝቡ ጋር በሰይጣናዊ ቅንዓት ተነሣሥተው በስቅላት ያስገደሉት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋው ከተቀበረም በኋላ ቅንዓታቸው ሊበርድ፥ ጭካኔያቸውም ሊረግብ አልቻለም፡ ያ፡ ያሠቃዩት ጌታ ስለፍጥረቱ ቤዛነት የመጨረሻው የፋሲካ በግ ሆኖ የተሠዋበትንና ይህን የመሰለው መለኮታዊ ፍቅር ተፈጽሞ ምስጢሩ የተከሠተበትን እንጨት እንኳ በርኅራኄያቸው ትተው ሊያልፉት አልፈለጉም። ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሠርቀው እንዳይወስዱትበሚል ምክንያት መቃብሩን እንዲያስጠብቅላቸው ወደጲላጦስ ሄደው በመማፀንና እርሱም ፈቃዳቸውን በመፈጸም በድኑን ሳይቀር እንዳልተዉት ሁሉ አሁንም በመስቀሉ ላይ የፈጸሙት ግፍ ከዚያ ያላነሰ፥ እንዲያውም የባሰና ወደር የማይገኝለት ሆኖ እንዲቀጥል ማድረጋቸውን እነሆ እንመለከታለን።

ይኸውም፡ መስቀሉ ደብዛው ሳይቀር ጨርሶ እንዲጠፋ ያደረጉበት መሠሪ ዕቅዳቸውና ክፉ ድርጊታቸው ነው። በዚህ ዕቅዳቸው መሠረት ማንም ሰው የራሳቸው የሆኑት ወገኖቻቸው እንኳ ሳይቀሩ ሊጠረጥሩ በማይችሉበት ሁኔታና ሥፍራ፡ መስቀሉን በድብቅ አስወስደው ቀበሩት ያም ሥፍራ ለከተማው የቆሻሻ መጣያ የተመደበው ቦታ ነበር።

በዚህ ድርጊታቸው ሦስት እኩይ ዓላማዎቻቸውን የፈጸሙ መስሏቸው ነበር። ከእነዚህ ዓላማዎቻቸው መካከል፦

፩ኛ፦ የሰማይና የምድር ፈጣሪና ጌታ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው የተቆረሰበትንና ክቡር ደሙ የፈሰሰበትን ምሥዋዕ (መሠዊያ) መስቀሉን ማርከስ ሲሆን፥

፪ኛ፦ ሕዝቡ ሁሉ የቤቱንና የከተማውን ጥራጊና ቁሻሻ በየቀኑ ያለማቋረጥ በማፍሰስና በመጣል መቀበሩን ማንም ሊያውቅ እንዳይችል፡ ምናልባት ቢታወቅ እንኳ ምን ጊዜም ተቆፍሮ እንዳይገኝና እንዳይወጣ ማድረግ ነው፥

፫ኛ፦ መስቀሉን እንዲህ አድርገው በሚቀብሩበት ጊዜ የክፋታቸው መጠን ምን ያህል የጸና መሆኑን የሚያመለክተው ሌላው ገጽታ ይታያል፡ ይኸውም፡ ዕፀ መስቀሉ ምናልባት ተቆፍሮ የተገኘ እንደሆን የዓለም መድኅን የተሰቀለበት እውነተኛው እንጨት የትኛው እንደሆነ ተለይቶ እንዳይታወቅ ለማደናገር ሲሉ፡ በቀኝና በግራ የተሰቀሉትን ወንበዴዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወንጀለኞች ጭምር የተሰቀሉበትን እንጨት ከጌታ መስቀል ጋር ደበላልቀው እንዲቀበር ማድረጋቸው ነው።

ዕሌኒ ንግሥትና ልጇ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ

ነቢዩ ዳዊት፡ ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔርእንዳለው፡ እግዚአብሔር ፈቃዱን የሚፈጽምበት፡ ሥራውንም የሚሠራበት ጊዜ ስላለው የዚህ የመስቀሉ ክብርና ኃይል የሚገለጽበት ቀኑ፡ እነሆ ደረሰ። ያም ቀን ምድረ ከነዓንን በማጠቃለል፡ በማእከላዊው ባሕር አካባቢ ያለውንና በዘመኑ ሥጋዊው ሥልጣኔ ዳብሮበታልየተባለውን ዓለም በቄሣርነት የገዛው ቆስጠንጢኖስ በ፫፻፳፭ ዓ.. በእናቱ በንግሥት ዕሌኒ አማካይነት የክርስትናን እምነት ለመቀበል፡ ራሱን ያበቃበት ጊዜ ነበር። በዚያው ዓመት ሃይማኖታዊት የሆነችው ይህችው ንግሥት እናቱ፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ አድጎና ኖሮ ተሰቅሎና ሙቶ ተነሥቶና ዐርጎ ተልእኮውን በማከናወን ዘለዓለማዊ የምሕረት ጸጋውን ለሰው ልጆች በቃል ኪድን የሰጠባቸውን ቅዱሳት መካናት ትሳለም ዘንድ ልቦናዋ ተነሣሥቶ ወደ ኢየሩሳሌም እንድትጓዝ ሆነ።

ዕሌኒ ንግሥት፡ ኢየሩሳሌም ገብታ ቅዱሳት መካናትን እየተዘዋወረች ከጎበኘች በኋላ ስለጌታ ቅዱስ መስቀል በጠየቀች ጊዜ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ባለመታወቁ እስከዚያን ቀን ድረስ የመስቀሉ ነገር የተሠወረ ምሥጢር ሆኖ እንደሚገኝ ተነገራት። በዚያን ጊዜ መስቀሉን በሚመለከት በመንፈሳዊ የፍቅርና የቅንዓት እሳት በነደደ ልቦናዋ የጌታን ሕማማቱንና የተናገራቸውን ቃላት በማዘከር ወደፈጣሪዋ የእንባ ጸሎትን አቀረበች፡ በእርሷ በኩል ምን ማድረግ እንደሚገባት ያመለክቷትም ዘንድ ወደቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ካህናት በየቦታው ወደዘጉ ባሕታውያን ሳይቀር እየላከች አስጠየቀች።

ከእነርሱም ያገኘችው መልስ፡ ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበውና በምሕላ ተጠምደው የዘጉትና የበቁትም በየበዓታቸው ተጠናክረው ኹሉም በያለበት ጾምና ጸሎት በማድረስ፡ መንፈስ ቅዱስ ምስጢሩን እንዲፈታው መጠየቅ መሆኑን የሚያመለክት ነበረ። እርሷም ይህ የተባለው መንፈሳዊ ምግባር ራሷ ጭምር በተካፈለችበት እንዲካሄድ አድርጋ የእግዚአብሔር ጽድቅ የተገለጸበትንና መልካም የምሥራቅ ፍሬ የሆነውን ከዚህ የሚከተለውን መመሪያ ለማግኘት በቃች። ይህም፡ ለመሥዋዕት እንደሚደረግ፡ እንጨት ተረብርቦ እንዲነድና በዚያ ላይ በሱባዔና በምሕላ የተጸለየበት ዕጣን ተጨምሮ ጢስ ቅታሬው ወደሰማይ ከወጣ በኋላ ወደምድር ተወርውሮ የሚተከልበት ያ ቦታ ጌታ የተሰቀለበት እውነተኛው ዕፀ መስቀል የተቀበረበት ሥፍራ መሆኑን አረጋግጦ የሚያሳይ ምልክት ይሁናችሁ!” የሚል ነበር።

በዚህ መሠረት መንፈሳዊቷ ንግሥት ይህንኑ መመሪያ በመከተል የታዘዘው ውጤት ታየ! ከሚነድደው እሳት ተነሥቶ፡ ወደሰማይ የወጣው የዕጣኑ ጢስ ቅታሬ ወደምድር ተመልሶ ከተራራማነት መጠን ደርሶ በነበረ በአንድ ጉብታ ላይ እንደጦር ተወርውሮ ተተከለ! ይህ ተአምር የታየበት ዕለት መስከረም ፲፯ ቀን ፫፻፳፮ ዓ.. ነበር፡ በዚያ ተራራ ላይ የሚደረገው ቁፋሮ በዚሁ ቀን ተጀምሮ ወደጥልቅ እየወረደ ሲቀጥል ከቆየ በኋላ፡ በመጋቢት ፲ ቀን መስቀሎች ተከማችተው ከሚገኙበት ዐዘቅት ተደረሰ!

በዚያ ዐዘቅት ውስጥ ከነበሩት፥ ሳይበሰብሱና መሬት ሳይበላቸው ከተረፉት ጥቂት መስቀሎች መካከል፡ ለካ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍጥረቱ ቤዛ ኾኖ ደሙ የፈሰሰበት እውነተኛው ዕፀ መስቀል አብሮ ይገኝ ኖርዋል! ነገር ግን የትኛው እንደሆነ ለይቶ ለማወቅ እጅግ አዳጋች ሆነ! ይሁን እንጂ፡ ይህን ችግር ለመፍታት ረዥም ጊዜን አልወሰደም፡ ብዙ ድካምንም አልጠየቀም፡ አማናዊው ቅዱስ መስቀል የተለያዩ ተአምራትን በመፈጸምና ራሱን ከሌሎቹ ለይቶ በማቅረብ ማንነቱን በታላቅ ኃይል ገልጦ ሊያሳይ ችሏልና።

ዛሬም፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደመራእና መስቀልእያልን በየዓመቱ የማንከብረው በዓል መነሻና ዓላማው ይህ መታሰቢያነቱም ለዚህ መሆኑን እናውቀዋለን።

ንግሥት ዕሌኒ እውነተኛ ክርስቲያንና ጽኑ ሃይማኖታዊት ናት፡ ለክርስቲያኖችም ሁሉ ባለውለታ ነች። በተለይም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን፤ ንግሥት ዕሊኒ በኢየሩሳሌም ባሳለፈችው የጥቂት ዓመታት ቆይታዋ የመጣችበትን ቅዱሳት መካናትን የመሳለም ዓላማዋንና ታላቁ ትሩፋትዋ የሆነውን የጌታን ቅዱስ መስቀል አስቆፍሮ የማውጣት ተል እኮዋን ማከናወን ብቻ ሳይሆን በዚሁ ጎልጎታ በተባለውና መስቀሉ በተገኘበት ቦታ ላይ የኢየሩሳሌምን ቤተ ክርስቲያን በአምስት ዓመታት አሠርታ ጨረሰች አሠርታም እንደጨረሰች፡ ምዕራቡን ለሮም (ለግሪኮች) ምሥራቁን ለሓበሾች (ለኢትዮጵያውያን) ሰጠች።

ይህ የኾነው ያለምክንያት አልነበረም። ኢትዮጵያውያን ጥንት ኢየሩሳሌምን ከቈረቈረው አባታቸው ከመልከ ጼዴቅ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያዊት ንግሥታቸው ማክዳ ከዚያም ታላቁ እስክንድር እስከተነሣበት ዘመን ድረስ ከትውልድ ወደትውልድ እየተላለፉ፡ በውርስ የደረሷቸው በኢየሩሳሌም ያሉት የዐፅመርስት ቦታዎችና ንብረቶች በይዞታቸው ሥር ተጠብቀው ይኖሩ ነበረ፤ በእስክንድር ዘመን ግን በእርሱ ሥልጣን ከተተኩት ከአራቱ የጦር አዝማቾቹ አንዱ ወራሽ የነበረው ፬ኛው አንጥያኮስ ኤጲፋንዮስ የተባለው አረማዊ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ፩፻፺፰ ዓመት፡ ኢየሩሳሌም ገብቶ ታላቅ ዕልቂትንና ብርቱ ጥፋትን አደረሰ፡ ከዚህ በኋላ ከክርስቶስ ልደት በፊት፡ በ፩፻፺፯ ዓመት፡ መቃብያን በእርሱ አገዛዝ ላይ በዓመፅ ተነሥተው እስኪያስወግዱት ድረስ እነዚህ የኢትዮጵያ ይዞታዎች በዚያ ከሚገኙት ቅዱሳት መካናት መካከል ጠፍ ሆነው ቆይተው ስለነበረ ነው።

ይህን እውነታ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ማስረጃ ያረጋግጠዋል። ስሙ ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ቆስጦንጢኖስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ፫፻፳፭ ዓ.ም ግድም በሮም (በቍስጥንጥንያ) ነግሦ እናቱን ወደ ኢየሩሳሌም ልኳት እርሷም ቀደም ብሎ እንደተገለጸው የመጣችበትን የተቀደሰ ዓላማዋን ታላቁን ተልእኮዋንና የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራዋን አከናውና እንደፈጸመች ወዲያው በጊዜው ለነበሩት ክርስቲያኖች ቦታ በምትሰጥበት ጊዜ፡ አብርሃ ወአጽብሓ የተባሉት የዘመኑ የኢትዮጵያ ነገሥታት ወደቆስጠንጢኖስና ወደእናቱ ንግሥት ዕሌኒ እንዲህ ሲሉ ላኩ፦

በኢየሩሳሌም ገዳመ ንጉሥ” [ኋላ በእስላሞች ጊዜ ዴር ሡልጣን] የተባለ አንድ ቦታ የአሕዛብ ነገሥታት ኢየሩሳሌምን እስኪያጠፏት ድረስ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ነገሥታት እጅ እንደነበረ ከታሪክ አይታችሁ፡ ከሽማግሌም ጠይቃችሁ እንድትመልሱልን እንለምናችኋለን።

ከእናንተ በፊት የነገሡ አሕዛብ እግዚአብሔርን የማይፈሩ ስውን የማይፈሩ ነበሩና፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ አማኝ ንጉሥ እስኪያነግሥ ድረስ ዝም አልን። አሁን ግን እግዚአብሔርን የሚፈራ ለሕዝበ ክርስቲያን የሚራራ ርስትን የሚተክል እንጂ የማይነቅል ቆስጠንጢኖስ የሚባል ደግ ነገሠ!’ የሚል ዜናን ብንሰማ እጅግ በጣም ደስ አለን።

ስለዚህ አንቺም ክብርት ንግሥት ሆይ፥ ደግ ክርስቲያን መኾንሽንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማፍቀርሽን ሰምተናልና የናት ልመና ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስ!’ እንደሚባለው ለንጉሡ ልጅሽ ነግረሽ፡ ርስታችንን አስመልሽልን!’ ብለው ወደ ዕሌኒ ንግሥት ላኩ።

እርሷም ይህንኑ ወደልጇ ወደንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ልካ አሳወቀችው። ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም የኢትዮጵያ ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሓ የላኩትን ቃል አይቶ ከታሪክም ተመልክቶ ከሽማግሌዎችም ጠይቆና ተረድቶ የእናቱንም ምክር ሰምቶ በደስታ እሺ!” አለ።

ይኽው በኢየሩሳሌም ቅዱሳት መካናት የኢትዮጵያውያን ርስታቸው የኾነው ቦታ በንጉሥ ቆስጠንጢኖስና በእናቱ በንግሥት ዕሌኒ ትእዛዝ እንደቀድሞው ለኢትዮጵያውያን እንዲመለስ ተደረገ። ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት መኖሪያ ቤት ሠርተው ባገኙት ቤተ ጸሎት እያገለገሉ ቆዩ። ይህም የኾነው ከ፫፻፳፰ ዓ.ም ጀምሮ ነው። እስከዘመነ ተንባላትም ድረስ (ማለትም እስላሞች ሥልጣን እስከያዙበት ጊዜ ድረስ) ከሦስት መቶ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ በሰላምና በዕረፍት ኖሩ።

የመስቀሉ ነገርና ኢትዮጵያዊው አጼ ዳዊት

ይቀጥላል

__

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: