ጅቡቲን አንርሳ
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on April 27, 2014
እኛ ኢትዮጵያን በሀገራዊ ደረጃ ደግመን ደጋግመን ከምናሳያቸው ተገቢ ያልሆኑ አደገኛ ድክመቶች መካከል የሚከተሉትን መታዘብ ይቻላል፦
፩. ለአለፈው ታሪካችን ተገቢውን ትኩረት አለምስጠታችን፣ በተለይ ከጠላቶቻችን በኩል የደረሱብንን በደሎች ቶሎ መርሳታችን – ‘ታሪክ ምን ይሠራል?’ ይባል የለ ትምህርት ቤቶች አካባቢ
፪. ለራሳችን ሳይሆን ለባዕዳውያኑ / ለባዕዱ አስቀድመን አክብሮትና አድናቆት መስጠታችን። የስነምግባራዊ እጢአችን የሚቀሰቀሰው ለወገን ሳይሆን ለባዕዳውያኑ መሆኑ
፫. አርቀን ማየት አለመቻላችን
ከታሪክ ለመማርና አርቀን ለማየት ካለመቻላችን የተነሳ በጉልበተኞቹ ጠላቶቻችችን ጫማ ሥር በተደጋጋሚ እየወደቅን እራሳችንን ስናደክምና ስንጎዳ ይታያል። ቀላል ባቡር ለመሥራት ብዙ ወጭ የወጣበት አስፋልት ይቆፈራል። የውጭ ገንዘብ ለማግኘት እየተባለ ብርቃማና ውድ የሆኑትን የእህል ዘሮች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለጠላቶቻችን እንልካለን፤ በዚህም ወደፊት የሚፈታተኑንና የሚጎዱንን በሽተኞች እንፈውሳለን፤ እናጠነክራለን። ባንኮቻችን ፔትሮዶላሮችን ለመሰብሰብ ይበቁ ዘንድ ጤናማ ዜጎቻችን ወደ አረቡ አገራት ይላካሉ፤ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ግን ደካክመው፣ ተጎሳቁለውና ተኮላሽተው ወደ አገራቸው ባዶ እጆቻቸውን ይመለሳሉ፤ ለመንግሥትና ለአገር፣ ለቤተሰብና ለሕዝብ ኃሳብና ሸክም ስለሚሆኑም በብዙ እጥፍ የሚገመት ወጭ ለማውጣት እንገደዳለን። በተለይ ከመንፈሳዊ ሕይወት አንፃር ለሁሉም የሚያስከትለው ውድቀት በጣም ከባድ ስለሆነ የወገኖቻችን ወደ አረቡ ዓለም መሄድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የምናየው ነው።
ጠላቶቻችን የሦስት መቶ ዓመታት ዕቅዶች በመያዝ ከመቃድሾ እስከ ካርቱም፣ ከኤደን እስከ ጂቡቲ ያሉትን የኢትዮጵያ ግዛቶች አንድ ባንድ ሸርሽረው ወሰዱ፣ ከዚያም ሰሜን ኢትዮጵያን ገነጠሉ፣ ቀዩንም ባሕር በመቆጣጠር መተንፈሻና መፈናፈኛ አሳጡን።
አባቶቻችን ልክ ጂቡቲን ለፈረንሳይ አሳልፈው እንደሰጡት፣ የዛሬው ትውልድም ድንግል መሬቶችን ለሳዑዲ ያኮናትራል። ይህም ጉዳይ፡ ወይ ለጊዚያዊ መፍትሔ ሲባል በጥልቅ አልታሰበበትም ወይም ሌላ ምስጢር አለ። የጂቡቲ ጉዳይ ብዙ ትምህርቶችን ሊሰጠን ይችላል። እነ ፈረንሳይ ጂቡቲን ሲኮናተሩ ከመቶ ዓመታት በኋላ ቦታው የስትራቴጂካዊ ጥቅም ይኖረዋል ብለው በማሰብ ነበር። ኢትዮጵያ ጂቡቲን ማጣቷ እንዳይበቃ ለኢትዮጵያ ብዙ ወጭ የምታስወጣ ወደባማ ከተማ፣ ለሚተናኮሉን ኃያላን መንግሥታት ድገሞ ቁልፍ የጦር ሰፈር ለመሆን በቅታለች።
እዚህ ቪዲዮ ላይ እንደምናየው የምዕራባውያኑ (NATO) ጦር ሠራዊት ባሁኑ ጊዜ ጂቡቲ ውስጥ በመስፋፋት ላይ ነው። የቢቢሲ ቃል አቀባይ “ባካባቢው የሚገኙትን ሽብር ፈጣሪዎች ለመከታተል” በሚል ሰበብ ጂቡቲ የሰፈረውና በአሜሪካ የሚመራው የምዕራባውያኑ ሰራዊት “ምስጢራዊ” የሆነ ተልዕኮ እዚያ እንዳለው አልደበቀም። ይህ ምስጢራዊ ተልዕኮ ምንድን ነው? አሜሪካዊው ኮማንደር “ዓላማችን ጥሩዎችን ለመርዳት ነው” ሲሉ “ጥሩዎቹ” እነማን ይሆኑ? በጂቡቲ ተመሥርቷል የተባለው የጦር ኅብረትስ ለምንድን ነው የነጮች ብቻ ኅብረት የሆነው? በአፍሪቃ ምድር፣ ያውም ኢትዮጵያ በር! እንዴት ኢትዮጵያውያን / አፍሪቃውያን ሊሳተፉ ብሎም ምስጢሩን ሊካፈሉ አልቻሉም?
__
Leave a Reply