እንኳን ለብርኃነ ልደቱ በሰላም አደረሰን!
የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት (ልደተ እግዚእነ) በማስመልከት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያስተላለፉት መልዕክት፦
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን!
–በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ
–ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ
–የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረኡ የቆማችሁ
–በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ
–እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፣
ወልድ ተብሎ ውሉድ እንድንባል ላበቃን ለጌታችን ለአምካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!
“ወናሁ ትፀንሲ ወትወልዲ ወልደ ወትሰምዪ ስሞ ኢየሱስ ዘውእቱ ያድኀኖሙ ለሕዝቡ እምኃጢአቶሙ፤ እነሆ ትፀንሻለሽ፣ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፣ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና፣ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ” {ሉቃ1 ፥ 31 ፤ ማቴ 1 ፥ 21]
ሁላችንም እንደምናውቀው፤ ዘላለማዊና ቀዳማዊ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰው ሆኖ እንዲወለድ ምክንያት የሆነው፣ የሰው ኃጢአት ነው።
ሰው በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይቶ ክብሩን ካጣ በኋላ፣ በነፍሱም ሆነ በሥጋው፣ ለአጠቃላይ ውድቀት ተዳረገ፤ ንጹሕ የነበረ ባህርዩ እንደ ሰኔና እንደ ሐምሌ ጎርፍ ደፈረሰ፤ የኃጢአት ድፍርሱም እየባሰና እየከፋ ከመሄድ በቀር፣ መሻሻል አላሳየም፤ ይሁንና የክብር አምላክ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን፣ ለክብር በክብር የፈጠረውን የሰው ልጅ፣ እንደ ወደቀ ሊቀር አልፈለገምና፣ የመዳኛ ዘዴ አበጀለት።
አምላካችን እግዚአብሔር ሰውን የማዳን ሥራው፦
- መቼ?
- በማን?
- የት?
- እንዴት?
እንደሚከናወን፣ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሙሉ በትንቢት፣ በምሳሌ፣ በራእይና በቀመረ ሲባኤ፣ በቅዱሳን ነቢያቱ አማካኝነት፣ ለዓለም ሲገልጽ ቆየ።
በእርሱ የተያዘው ቀጠሮ ሲደርስ፣ በፊቱ የሚቆመውን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን፤ ወደ ድንግል ማርያም ላከ። ቅዱስ ገብርኤልም፣ ከእግዚአብሔር ንገር ተብሎ የተላከበትን መልእክት ይዞ፣ ወደ ድንግል ማርያም መጣ፤ እንዲህም አላት፡ “እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና፣ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፤ እርሱ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ አላት።“
ከዚህ አገላለጽ በመነሣት፣ ፍሬ ነገሩን ስናስተውል፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም የሚወለደው ሕጻን፦
- ዕሩቅ ብእሲ (ተራ ሰው) ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር መሆኑን
- የስሙ ትርጓሜም መድኃኒት ማለት መሆኑን
- መድኃኒትነቱም ለሕዝቡ ሁሉ መሆኑን
- ሕዝቡን የሚያድናቸውም ከኃጢአታቸው መሆኑን
በማያሻማ ሁኔታ ማወቅ ይቻላል።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ፣ ምእመናንና ምእመናት
የጌታችን መድኃኒትነት ድንበር የለሽና፣ በሁሉም በሽታዎች ላይ የሚሠራ ቢሆንም፣ በዋናነ ግን፣ በትልቁ የኃጢአት በሽታ ላይ ያነጣጠረ መድኃኒት መሆኑን፣ በተጠቀሰው ኃይለ ቃል መረዳት ይቻላል። ምክንያቱም በዓለም ላይ የሚታየውን ክፉ በሽታ ሁሉ፣ ሰበብ በመሆን ጎትቶ ያመጣብን ይህ ኃጢአት ነውና፣ ጌታችን በዋናነት እርሱን ለመደምሰስ መምጣቱን ለማሳየት፣ ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል ተብሎ በግልጽ ተለይቶ ተነገረ፤ በሽታው ትልቅ መሆኑን የምንረዳው፣ ትልቅ ዋጋ ያለው መድኃኒት፤ ያውም የእግዚአብሔር ልጅን ያህል፣ ለመሥዋዕትነት ያስፈለገው በመሆኑ ነው።
ለመሆኑ የኃጢአት በሽታ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድን ነው? ያልን እንደሆነ፤ ሰውን ከእግዚአብሔር በማራቅና እግዚአብሔርን በማሳጣት፣ ሰውን ማዋረድ፣ ማጎሳቆልና መግደል ነው፤
ሰው እግዚአብሔርን ካጣ፣ ሁሉንም ያጣል፣ አዳም አባታችንና ሔዋን እናታችን ያጡም ይህንን ታላቅ ሀብት ነበር፤ እግዚአብሔርን ሲያጡ፤ ሁሉንም አጡ፤ ኃጢአተኞችም ሆኑ፤ ኃጢአተኛ ማለት ያጣ፣ የነጣ ማለት ነው፤ ምንን ያጣ? እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ ያጣ ማለት ነው፤
ሰው ከእግዚአብሔር ከተለየ፦
- ሕይወት የለም
- ሰላምም የለም
- ክብርም የለም
በአጠቃላይ መልካም የሆነ ነገር ሁሉ የለም፤ ሊኖር የሚችለው ተቃራኒው ነው፤ እርሱም፦
- ሞት
- በሽታ
- ድህነት
- ጠብ
- መለያየት
- ውርደት
የመሳሰለው ክፉ ነገር ሁሉ ነው ሊኖር የሚችለው፤
ከዚህ አንጻር ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ፣ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል ሲባል፣ በዋነኛነት እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ ከማጣት ያድናቸዋል ማለት ነው።