Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

  • December 2013
    M T W T F S S
     1
    2345678
    9101112131415
    16171819202122
    23242526272829
    3031  
  • Archives

  • Categories

  • Recent Posts

Archive for December 28th, 2013

የታኀሣሥ ገብርኤል — Tahisas Gebriel

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on December 28, 2013

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትከሚለው ፡ የንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ መጽሓፍ የተወሰደ

ከከበረ ሰላምታ ጋር!

BisrateGabriel6

በዚህ በታኀሣሥ ወር በ፲፱ነኛው ቀን የሚውለው የ ታኀሣሥ ገብርኤልበዓል የሚከበርበት ምክንያት እንዲህ ነው፦

እግዚአብሔር በሙሴ መሪነት የእሥራኤልን ሕዝብ በግብፅ አገር ይገኙበት ከነበረው የባርነት አገዛዝ ነጻ አውጥቶ ቤተ መቅደሳቸውንና ከተማቸውን በኢየሩሳሌም አድርገው በምድረ ከነዓን እንዲኖሩ አበቃቸው። እነርሱ ግን ባካባቢያቸው ያሉትን አሕዛብ እየተከተሉ አምልኮ ባዕድን በመፈጸም አምላካቸውን እግዚአብሔርን አሳዘኑት። በነቢያቱ ቢመክራቸውና ቢገሥፃቸውም በዚያ ኃጢአታቸው እየጨመሩበት ከመኼድ በቀር ከበደላቸው ተጸጽተው ሊመለሱ ጨርሶ የማይቻል ኾነ።

በዚህ መልክ በፈጣሪያቸውና ከእርሱ ጋር በተጋቡት ቃል ኪዳናቸው ላይ በሥውርና በገሃድ ያካኺዱት የነበረው ክህደት ዓመፅና አመንዝራነት በመጨረሻ ጽዋው ስለሞላ እግዚአብሔር ለዚህ ድርጊታቸው ምስክር የኾነችው ታቦተ ጽዮን ከእሥራኤላዊው ንጉሥ ከሰሎሞንና ከኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ከማክዳ በተወለደው በቀዳማዊ ምኒልክ አማካይነት በቅድሚያ ወደ ኢትዮጵያ እንድትሄድ አደረገ። ከዚያ በኋላም ያወረሳቸውን አገርና ከተማ ወርሮ ይበዘብዝ ዘንድ አረማዊውን ንጉሥ፡ ናቡከደነፆርን ታላቅ የሠይፍ ኃይልን አስታጥቆ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፡ እርሱም በዚያ የቅጣት ተልእኮውን እንዲፈጽም፡ ኃጢአተኛውንም የእሥራኤል ትውልድ ፈጅቶ የተረፉትን በምርኮ ወደ ምድሩ ወደ ባቢሎን እንዲወስዳቸው ለስደትም እንዲዳርጋቸው አሠለጠነው።

ለዚያ ስደት ከተዳረጉት እሥራኤላውያን መካከል በሃይማኖታቸው የጸኑና በምግባራቸው የተጠናከሩ አካኼዳቸው ከነቢዩ ዳንኤል ጋር የሆነ፡ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል የተባሉ መንፈሳውያን ወጣቶች ነበሩ። እነዚህ ሠለስቱ ደቂቅየተባሉት ሦስት ልጆች፡ በእውቀታቸውና በብልህነታቸው ተመርጠው የንጉሡ ሹማምንት ሆነው ያገለግሉ ነበር።

የኋላ ኋል ግን የአገሩን አማልክት እንዲያመልኩ ንጉሡ ላቆመውም ጣዖት እንዲያሰግዱ ያን ባያደርጉም በአዋጅና ባደባባይ እየነደደ ባለ አስፈሪ የእሳት ነበልባል ውስጥ የሚጣሉ መሆናቸውን የሚገልጽ የፈተና ጥያቄ ከንጉሡ ቀረበላቸው። እነርሱም ለገንዘብና ለሹመት ጓጉተው የንጉሡን ቍጣም ፈርተው አምላካቸውን የማይክዱ ሃይማኖታቸውንም የማይለውጡ መሆናቸውን በመግለጽ፡ ንጉሥ ሆይ! የምናመልከው አምላካችን ከእጅህም ሆነ፡ ከዚህ ከሚነድደው የእሳት ነበልባል ሊያድነን ይችላል ባያድነንም እንኳ አማልክትህን እንዳናበልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ጣዖት እንዳንሰግድለት እወቅ!” ሲሉ በድፍረትና በቆራጥነት መልስ ሰጡት።

በዚህ ጊዜ ፍርዱ እንዲፈጸምባቸው ከንጉሡ ታዝዞ ሦስቱም ገድለኞች በሚነድደው እሳት ውስጥ ተጣሉ። ወደ እሳቱ ሊጥሏቸው የወሰዷቸው ኃያላንም በነበልባሉ ብርቱ ወላፈን እየተቃጠሉ ሞቱ።

BisrateGabriel13

Additional pictures of Bisrate Gebriel Orthodox Tewahedo Church

ወደ እሳቱ ውስጥ ታሠረው የተጣሉ እኒህ መንፈሳውያን አርበኞች ግን የእግዚአብሔር መልአክ እሳቱን አቀዝቅዞላቸው በነበልባሉ መካከል ወዲያ ወዲህ ሲመላለሱ ከመታየት በቀር በአካላቸው ቀርቶ በልብሳቸው ላይ እንኳ አንዳችም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከተፈረደባቸው የቃጠሉ ሞት ድነው በደህና ሊወጡ ችለዋል፡ ይህንም የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከነፆር ተደነቀ፡ ፈጥኖም ተነሳ፡ አማካሪዎቹንም ሦስት ሰዎችን አሥረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? …እነሆ፡ እኔ፡ የተፈቱ፡ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን አያለሁ ምንም አላቆስላቸውም፡ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል። ብሎ መለሰ።የሚለው የመጽሓፍ ቃል ያረጋግጣል።

የአራተኛው መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል፡የተባለው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል መሆኑን ከትውፊታችን አግኝተነዋል።

በሃይማኖት ሳይወላውሉ በምግባር ተጠናክረው እስከመጨረሻው ማለትም የሞት ጽዋን ለመቀበል ተዘጋጅቶና ቆርጦ እስከመቅረብ ድረስ በጀመሩት ገድል ጸንቶ መገኘት የሚያስከትለው ውጤትና የሚያስገኘው ፍሬ በነፍስ ብቻ ሳይሆን የሥጋ ሞትን ችምር በማስቀረት የምሕረት ሕይወትን በክፋት ኃይላትም ላይ ድልን የሚያቀዳጅ የመላእክት ተራዳኢነትን መሆኑን በዚሁ በታኀሳስ ፲፱ ቀን የምናከብረው የ ታኀሣሥ ገብርኤልበዓል ያስታውሰናል፡ ያስተምረናልም።

__

Posted in Ethiopia, Faith | Tagged: , , , , , | Leave a Comment »

 
%d bloggers like this: