የዓለም ፍጻሜ
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on April 6, 2013
በ ማ/ቅዱሳን
የሰው ልጅ ከሥነ ፍጥረት መነሻ ጀምሮ ስለ ራሱ መጨረሻና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምንነት ማወቅን እንደሚሻ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ ከነዚህም በተለይ ቤተ ክርስቲያን በደብረ ዘይት እለት የምታስተምረው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት’ የዓለሙ ፍሳሜስ ምልክቱ ምንድነው?/ማቴ. 24፥3/’ በማለት የጠየቁት ጥያቄ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ከመለሰላቸው ዋናውና ቀዳሚው የምጽአቱ ምልክት የሐሳዊ መሲህ መምጣት ነው፡፡ ሐሳዊ መሲሕ ማለት በቀጥታ ትርጉሙ ሐሰተኛ የሆነ በስሙ ማለትም በኢየሱስ፣ በክርስቶስ፣ በአምላክ ስም የሚመጣ የክርስቶስ ተቃዋሚ ማለት ነው፡፡ ትርጉሙን አስፍተን ስናየው፣ ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ተያያዥ የሆኑና ያልሆኑ በዓለም እየተካሄዱ ያሉ ሐሰተኛ ጉዳዮችንና የጥፋት መንገዶችን ያጠቃልላል፡፡ የሐሳዊ መሲሕ የጥፋት ሥራዎች ሳያውቁም ሆነ በተለይ ሆን ብለው በዓለማውያንና በክፉ መናፍስት ተከታዮች እየተፈለሰፉ በሚከሰቱ ሁኔታዎች የሚካሄዱ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የተገኙ የሃይማኖት የሥነ ተፈጥሮ የጋብቻና የመሳሰሉ ድንበሮች ማፍለስን ዓላማ ያደረጉ፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ባህል፣ ሰብአዊ ክብርና የእድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ ሁሉ ከሐሳዊ መሲሕ መደብና ከዓለም ፍጻሜ ምልክትአንጻር የሚታዩ ናቸው፡፡ በዝርዝር ለማየት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፣
- የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ
- የሥነ ተፈጥሮ ሕግ ድንበር መጣስ
- በጋብቻ ላይ የሚደረግ ርኩሰት
- መንፈሳዊ ባህል፣ የክህነት ክብር፣ ሰብአዊ ክብርና የእድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር ማጥፋት
1. የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ፡– ”አባቶችህ ያኖሩትን /የሠሩትን/ የቀድሞውን የድንበር ምልክት አትፍልስ” ምሳ.22፥28፣ 23፥10 አፈጻጸሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት እንዳያውቁ ከማድረግ ይጀምራል፡፡ከዚህም አንዱ ሐሳዊ መሲሕ በእግዚአብሔር ስም በተለያየ ሁኔታና መንገድ መገለጥ ነው፡፡ ”እስመ ብዙሃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ፤ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ብዙ ሰዎች በኔ ስም ይነሣሉና” /ማቴ. 24፣5/፡፡ ይህም እንደ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና የቅዱሳን ሐዋርያት ስብከት መሠረት፣ ከክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ በኋላ የሚመጣ፣ ክርስቶስን የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ነው ብሎ የማይሰብክ ሁሉ፤ ሌላ አምላክን የሚሰብክ ሁሉ መደቡ ከሐሳዊ መሲሕ ትምህርት ይመደባል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በፊት ያለፉ፣ አምላክ ነን ብለው የተነሡ እንደ ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ /ሐዋ. ሥራ. 5፣36-37/ የመሰሉ ሁሉ ከዚያም በኋላ በየጊዜው የተነሡና በዚህም ወቅት የዋሁን ሕዝብ ”ኢየሱስ ነኝ፣ ኢየሱስ በኛ ዘንድ አለ” እያሉ የሚያጭበረብሩ ሁሉ ሐሳውያነ መሲሖች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ክርስቶስን ከአብ የሚያሳንሱ፣ ”ሎቱ ስብሐት” ነቢይ ነው ብለው የሚያምኑ፣ በመናፍስት አሠራር የሚጠነቁሉ፣ በማቴሪያሊስት /ቁሳውያን/ ወይም በኢቮሉሽን /በዝግመተ ለውጥ/ ትምህርት አምነው አምላክ የለም የሚሉ ሁሉ፣ ወዘተ የሐሳዊው መሲሕ አካላት ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ”ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንደማመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።” /1ዮሐ. 4፣3/ በማለት ይመሰክርባቸዋል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አሁንም በመልእክቱ ”ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።” /1ዮሐ. 2፥18/ ይለናል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የክርስቶስ ተቃዋሚ መምጣት የምጽአት ጊዜው መቃረብ ምልክት መሆኑን የማያሻማ ሀሳብ ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም የምጽአትን መቅረብ የሚያመለክቱ፣ ስለ ሐሳዊው መሲሕ እና ከርሱ ጋር ተያያዥ ስለሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ተዛማጅ የሆኑትን የሚከተሉትን ትንቢቶች እንመልከት፣
ሀ. ”የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።” /ራእ. ዮሐ. 13፥16-18/ የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ራእይን ሊፈታ ከሚችልበት ትርጉም አንዲት ቅንጣት ብቻ ከዘመኑ አንጻር ብናይ ’የሚናገር የአውሬው ምስል’ ማለትም ለሱ ያልተገዙትን ወይም ቁጥሩን ያልያዙትን የሚናገርባቸው፤ ምልክቱን ያልተቀበሉትን ሊገዙና ሊሸጡ እንዳይችሉ ያደርግል ማለት መኖር፣ መሥራት፣ መሸጥ፣ መለወጥ ወዘተ የሚያግዳቸው ሲል አሁን ባለን ወቅታዊ የዚህ ዓለም አኗኗር አንጻር ሲታይ ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ መታወቂያ ወረቀት፣ ፓስፖርት፣ ቪዛ፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወዘተ በዓለም አጠቃላይ አሠራር እና ባንድ ሰው የመኖር ማንነት ሚና ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ መታወቂያ ወረቀቶች የሌሉት ሰው ካለበት የትም መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ከዚህም በላይ ጉዳዩን ስናሰፋው በሰለጠኑት ዓለማት አሠራር የእያንዳንዱ ሰው የጣት አሻራ ኮምፒውተራይዝድ በሆነ መንገድ የተደራጀ በመሆኑ፣ እዚያ አደረጃጀት ውስጥ ካልተካተተ በቀር እዚያ ሀገር ሊኖር፣ ሊዘዋወር፣ ሊሠራ፣ ሊነግድ ወዘተ አይችልም፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ እዚህ የኮምፒውተር ድር አደረጃጀት ውስጥ ያለ ሰው የትም ዓለም ቢሄድ በጣቱ አሻራ ይታውቃል፡፡ በትንቢቱ” አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።” የሚለው ይህን የሚያደራጀው ጉዳዩን የሚያስተሳስረው ሌላ አካል ሳይሆን ሰው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት የሚለው ቁጥር የሰው ልጅ የጅማት ቁጥር ነውና፡፡
ለ. ሌላው የምጽአት መቃረብ ምልክት የሐሳዊው መሲሕ ዘመቻን አውቀው በድፍረት፣ ላላወቁት በረቀቀ መንገድ እግዚአብሔርን ያመለኩ አስመስሎ የእግዚአብሔርን ስም፣ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳንን፣ ባጠቃላይ በሰማይ የሚያድሩትን መስደብ ነው፡፡ እነዚህም ተግባራት በተለያዩ ዘመናት ሲፈጸሙ የቆዩ ናቸው ዛሬም ተጠናክረው እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ሩቅ ሳንሔድ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችንን እየተፈታተነ ያለው የተሐድሶ ሤራ ዋናው ተቃውሞው የወልድን አምላክነት፣ የድንግል ማርያምን ክብርና አማላጅነት፣ የታቦትንና የመስቀልን ክብር፣ የቅዱሳንን ክብርና አማላጅነት ነው፡፡ በመሆኑም ተሐድሶ በሥራው የአውሬው መንፈስ አራማጅና መንገድ ጠራጊ መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል፡፡ ”ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፡– አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።” /ራእ. ዮሐ. 13፣4.8/ እንዲል፡፡
ሐ. ሌላው በዓለም ላይ የሚታየው በሰዎች ዘንድ ክብር፣ ዝናና ታዋቂነትን ለማግኘት ሲባል ራስን ከፍ ማድረግና እንደ አማልክት መቁጠር ከሐሳዊው መሲሕ ያስመድባል፡፡ ከዚህ በተመሳሳይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደገለጸው የሰናዖር ሰዎችን ኀጢአት ስናሰተውል የተነሡበት ዋናው ነጥብ ’ስማችንን እናስጠራ’ የሚለው ነበር፡፡” ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ።” /ዘፍ. 11፥4/ ነው የሚለን፣ በዚህ እኩይ አሳብ ምክንያት እግዚአብሔር ቋንቋቸውን ደባለቀባቸው፡፡ የሰናዖር ሰዎች ያሰቡትናየተመኙት ትውልዱ እግዚአብሔርን ማድነቅ ትቶ፣ ለዘለዓለም ስማቸውን ሲጠራቸው፣ ሲያደንቃቸው መኖርን ነበር፡፡ ዛሬም ብዙዎቹ ይህንን የሰናዖርን ኀጢአትና የጥፋት ጉዞ እንደ ዓላማ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
2. የሥነ ተፈጥሮ ሕግ ድንበር መጣስ አንዱ የጊዜው መቃረብ ምልክት ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት ፍጹም በመሆኑ፣ ይህ ቀረህ፣ ይህ ይጨመርልህ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት፣ ሰው ለተለያየ ጥቅም በሚል ሰበብ ዝርያቸው የተለያዩ የሆኑትን ፍጥረታት ማዳቀልንና ማደበላለቅን ተያይዞታል፡፡እንስሳትና ተክሎችን ለማባዛት የማያደርገው ጥረትና የማዳቀል ዘዴ የለም፡፡ በተቃራኒውም የሰውን ቁጥር ለመቀነስ የማያደርገው ሩጫ የለም፡፡ በመሆኑም ውጤቱ የሰውን ቁጥር ለመቀነስ ሲባል በሚደረጉ ሕክምናዎች ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች ተዳርገዋል፡፡ በሚደረገውም ማበረታታት በሠለጠኑት ዓለም ብዙዎቹ የግብረ ሰዶም ፈጻሚና አስፈጻሚ ሆነዋል፡፡ ይህ አሠራር አምላክ የሠራውን የፍጥረት ሕግ በማጣጣል ሰው ላሻሽል ወደሚል ያዘነበለ በመሆኑ የሰውን ልጅ ቅጥ ያጣ ድፍረት ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሥነ ፍጥረቱን እንዲያደባልቁበት አይፈልግም፡፡እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ”ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ” /ዘሌ. 19፣ 19፤/ ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው።” /ዘሌ 20፣ 13/ በማለት ያሰተምረናል፡፡
3. በጋብቻ ላይ የሚደረግ ርኩሰትንስንመለከትም በየትኛውም ዓለም የፍርድ ቤቶች ትልቁ ሥራ ማፋታት ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ተጋቢዎች ባንድ ላይ እንዳይኖሩ አውሬው /አስማንድዮስ/ የጋብቻ ጠላት በመሆን ስለነገሠ ፈተናውን መቋቋም አልቻሉምና ነው፡፡ ስለዚህ አስማንድዮስ ከዛ ይልቅ ግብረ ሰዶምን እያበረታታ በአንዳንድ ሀገሮች እንደሚታየው ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር እያቆራኘ በቤተ ክርስቲያኖቻቸው” ጋብቻ እስከ መፈጸም አድርሷቸዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣” ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤ እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም።” /ሮሜ.1፥24-ፍጻሜ
Leave a Reply