Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on December 28, 2012
በ ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ነቢዩ ዳንኤል “ዐይኖቼንም አነሣሁ” አለና አስከትሎ “እነሆም በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ፡፡ አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፤ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፣ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ፡፡… ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኀይልም አልቀረልኝም፤ ክብሬም ወደ ውርደት ተለወጠብኝ ኀይልም አጣሁ፡፡ የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምደር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ” አለ፡፡(ዳን.10፡5-9)
ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ብሎ የተናገረው የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤልን አስፈሪ ግርማ በተመለከተ ጊዜ ነበር፡፡ የዚህ መልአክ ግርማ የአምላክን ግርማ ይመስላል፡፡ ይህን ለመረዳት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ መለኮቱ ለወንጌላዊው ዮሐንስ የተገለጠበትን መገለጥ መመልከት በቂ ነው፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእይ ስለተመለከተው የክርስቶስ ግርማ ሲናገር፡– “ከኋላዬም እንደ መለከት ድምፅ ያለ ታላቅ ድምፅን ሰማሁ፡፡…የሰው ልጅ የሚመስልን አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ የሚደርስ ልብስ የለበሰ ፣ ወገቡንም በወርቅ ዝናር የታጠቀ ነበር፡፡ ራሱና የራስ ጠጉሩም እንደ ነጭ የበግ ጠጉር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፡፡ እግሮቹም በእሳት የነጠረና የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ብዙህ ውኃ ድምፅ ነበረ፡፡”… ባየሁትም ጊዜ ከእግሩ ሥር ወደቅሁ አንደ ሞተ ሰው ሆነሁ” አለ፡፡(ራእይ.1፡2-17) በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ቅዱስ ገብርኤል በግርማው አምላኩን እንደሚመስል አንረዳለን፡፡ የስሙም ትርጓሜ የሚያስዳው ይህን እውነታ ነው፡፡ ገብርኤል ማለት አምላክ ወሰብእ ማለት ነውና፡፡
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “እነሆ ከዋነኞቹ አለቆች” አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ”(ዳን.10፡13) ብሎ በተናገረው ንግግሩ በመላእክት ላይ የተሾሙ ሌሎች አለቆች እንዳሉ ማስተዋል እንችላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቅዱሳን መላእክት ዘንድ ስላሉት ነገዶች ሲገልጽ “… በሰማይ ያለውን በምደር ያለውን የሚታየውንምና የማይታየውን መናብርትም ቢሆኑ አጋእዝትም ቢሆኑ መኳንንትም ቢሆኑ ቀደምትም ቢሆኑ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ” (ቈላ.1፡16)በማለት ይዘረዝራቸዋል፡፡ ከዚህ ተነሥተን መላእክት በተለያዩ ዐበይት ነገዶች የተከፈሉና ለእያንዳንዱም ነገድ የራሱ የሆነ አለቃ እንዳለው ማስተዋል እንችላለን፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ከእነዚህ ዐበይት የመላእክት ነገዶች መካከል አንዱ በሆነው አርባብ (አጋእዝት ወይም ጌቶች) /አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/ በሚባለው ዐቢይ ነገድ ላይ የተሾመ ሲሆን ከበታቹም የሚመራቸው ዐሥር ነገደ መላእክት አሉ፡፡
እንኳን ለሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በዓል በሰላም አደረሰን የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ምልጃና ጸሎት ይጠብቀን ለዘለዓለሙ: አሜን!!
__
Like this:
Like Loading...
Posted in Ethiopia, Faith | Tagged: Ethiopian Orthodox Tewahedo Faith, Miracles of St.Gabriel, Qedus Gabriel, St. Gabriel | Leave a Comment »