የወቅቱን የዓለማችንን ሁኔታ በቅርብ ለሚታዘብና አገራቱንም በደንብ ተዘዋውሮ ለመመልከት አጋጣሚው ያለው ሁሉ የመጀመሪያዋና የመጨረሻዋ የክርስትና ምድር ምናልባት ኢትዮጵያ አገራችን ብቻ ልትሆን እንደምትችል ለመመስከር ይችላል።
ምንም እንኳን ትውልዳችን ሞኛሞኝ፥ ደካማና ለጠላት በቀላሉ ተጋልጦ የሚኖር ትውልድ ሆኖ ቢታየንም፡ ጽኑ በሆነ የክርስቲያናዊ ሕይወት ጎዳና ተግቶ የሚጓዘው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ከምንገምተው በላይ በጣም ከፍ ያለ ነው። በአሁኑ ጊዜ በተለይ ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶች፡ እናቶችና ልጆች ናቸው የክርስትናችንና የኢትዮጵያውነታችን ጽኑ መከታዎች ሆነው የሚገኙት። ጠላቶቻችን አንዳንድ መንፈሰ–ደካማ የሆኑ ሴቶቻችንን እንደምሳሌ በመውሰድ የወገኖቻችንን ስም ለማጥፋት ይጥራሉ፡ እኛም በቀላሉ የምንሰማውና የምናየው ይህ ብቻ ስለሚሆን እህቶቻችን ሁሉ የተበላሹ እንደሆኑ አድርገን ለመውሰድ እንበቃለን። ይህ ግን እጅግ በጣም የተሳሳታና ከእውነትም የራቀ ነገር ነው። ሴቶቻችን ከምንግዜውም በበለጠ ጥልቅ መንፍሳዊ ጉዞ ላይ ይገኛሉ፥ ሴቶቻችን አስደናቂ በሆነና ትጋት በተሞላበት መልክ የዓብያተ ክርስቲያናቱን ግቢዎች ዕለት ተዕለት እየሞሉ ጸሎታቸውን ያደርሳሉ። ይህ ሁኔታ እስካሁን አለመታየቱና ተገቢውን ትኩረት አለማግኘቱ በጣም ሊያሳዝነን ይገባል።
ባጠቃላይ ግን፡ የኢትዮጵያ ወጣት በሚያገኘው አጋጣሚ ሁላ የክርስትና ሕይወቱን በሚገባ ለመኖር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። መንፈሳዊ ጦርነት ላይ እንገኛለንና፡ ክርስቲያኑ በየትምህርት ቤቱ፡ በየገባያው፡ በታክሲና በየአውቶቡሱ የቅዱሳንን ምስሎች በመለጠፍና መስቀልንም በማንጠልጠል ለጠላቶቹ ድምጽ–አልባ የሆነ ኃይለኛ መልእክት በማስተላለፍ ላይ ይገኛል። “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው” (መዝ.59:4)
ታዲያ ይህ በእንዲህ እንዳለ፡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የብዙኃን ዜና ማሰራጫዎች ደግመው ደጋግመው የሕዝቡን ኃይለኛ የልብ ትርታ ለማዳመጥ አሻፈረኝ ይላሉ፥ ክርስቲያኖችንና ክርስትናን፡ ማለትም፡ ኢትዮጵያውያንን በቸልታ ማለፉን ይመርጣሉ። የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፤ እንዲሁም ጋዜጦችና መጽሔቶች ሁሉ በክርስትና ላይ ለማመጽ በአንድነት ውል የገቡ ይመስላሉ፡ ከእሁድ እስከ እሁድ ያለማቋረጥ የሚያወሩት፡ የሚያሳዩትና የሚጽፉት ስለ ፖለቲካ፥ ስለ ገንዘብ፥ ስለ ዘፈንና ዳንኪራ ብሎም ስለ እንግሊዝ እግርኳስ ጨዋታ ብቻ ነው።
የክርስትና እምነታቸው በተሸረሸረባቸው የምዕራቡ ኢዱስትሪ አገሮች እንኳ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በየሰንበቱ የጸሎት ስነሥርዓት ከዓብያተ ክርስቲያናት በቀጥታ ያስተላልፋሉ። የክርስቲያኖች ደሴት በሆነችው ኢትዮጵያ ግን ቴሌቪዥኑ በቅዱስ ሰንበት ፈጣሪን በትንሹም ቢሆን በማስታወስ ፈንታ፡ እንደ “ኢትዮጵያን አይደል” ወይም “ፖሊስና እርምጃው” የመሳሰሉት ፕሮግራሞች ደጋግሞ ማቅረቡን ይመርጣል። ጸረ–ክርስትና፡ ጸረ–ክርስቲያን እየሆኑ በመጡት የአሜሪካ እና አውሮፓ አገሮች የዜና ማሰራጫዎች እንደ ‘ፋሲካ‘እና ‘ገና‘ ለመሳሰሉት በዓላት የሚሰጡት አትኩሮት አሁንም አልቀነሰም፤ ሪዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በዓላቱ ከመድረሳቸው ከሣምንታት በፊት ነው የገና ዜማዎችን የሚያሰሙት፥ ምርጥ የገና ዜማ ሰሌዳዎችንም ያወጣሉ፤ የሮማው ፓፓስ ሆኑ ነገሥታቱና የአገር መሪዎቹ ሁሉ ለሕዝቦቻቸው የሚያቀርቡትን መልዕክት በሬዲዮና ቴሌቪዥን በቀጥታ ያስተላልፋሉ። ቀንደኛ ኢ–አማንያን እንደሆኑ የሚታወቁት እንደ Bill Mahr የመሳሰሉት ታዋቂ አሜሪካውያን የቴሌቪዥን ሰዎች ሳይቀሩ “አሁንስ በዛ! ከቤተሰብ ጋር አብረን የምናከብረውን የገና በዓላችንንማ አንነጠቅም” በማለት እየመጣ ወዳለው አስከፊ ጊዜ ይጠቋቁማሉ።
ታዲያ በpolitical correctness (ይሉኝታ)በሽታ የተለከፈው የምዕራቡ ዓለም እንኳ ማንነቱን ገና ሙሉ በሙሉ ለመካድ ሳይነሳሳ፡ ለምንድን ነው የኛዎቹ መሪዎች፡ ጋዜጠኞችና ጣቢያዎቻቸው አባቶቻቸው ለታገሉለትና ለሞቱለት የክርስትና ሕይወት ግድየለሽነትን የሚያሳዩት? በትዕግስተኛውና በዝምተኛው ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን እያሳደረ የመጣውን ይህን ሁኔታ አይተው አስፈላጊውን የማሻሻያ እርምጃ ለመውሰድስ እስካሁን ለምን ተሳናቸው?
_____________________________________________________