*ከማሞ ውድነህ*
…ካለፈው የቀጠለ…
“አሁንኮ አባታችን ያቀረቡልዎ ክስ የደንከልን በር ለሃይማኖት ተግባር ነው ብላችሁ ከገዛችሁ በኋላ ለንግድ ሥራና ለመንግሥት መገልገያ እንዲሆን አደረጋችሁ፤ የትንባሆ ነገር በሕዝቡ ዘንድ እንዲለመድ አድርጋችኋል ነውና ለዚህ መልስ ይስጡ” ብለው ጠየቋቸው።
አባ ማስያስ በጸጉር የተሸፈነ የዱር ድመት የመሰለ ፊታቸውን ወደ ዕጨጌው ዘወር አድርገው፤
“እሳቸውኮ እኛን በሆነ ባልሆነ የሚወነጅሉን አገራችሁ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ተወዳጅታ በጥበብ እንዳትኮራ እንደ እነርሱ በመሳሰሉ ከእስክንድርያ በሚላኩ ሰባኪዎች አማካይነት አገራችሁ የግብጽ ጥገኛ ሆና እንድትኖር ከግብጽም ፈቃድ እንዳትወጣባቸው፡ በዚህ አገሩ የሚኖሩ እስላሞች ክርስቲያይኖች እንዳይሆኑባቸው የግብጽ ከዲብ ባለሟልነት እንዳይቀርባቸው ብለው ነው” ብለው ሲሳለቁ ዕጨጌውን ቁጣ ቱግ አድርጎ አስቆጣቸውና፤
“ስሙ ወይ ማስያስ! ማንነትዎንኮ አሳምሬ ደርሼበታለሁ! የጣሊያኑ ንጉሥ ነፍስ አባት አይደሉም? ይህን ያምናሉ? ወይስ ይክዱኛል?” ብለው አፈጠጡባቸው።
“ይኽ ነገር እውነት ነው?” ብለው ዮሐንስም ተጨመሩ። የችሎቱ ፍጥጫ ከአባ ማስያስ ላይ ተከመረ።
“ብሆንስ ምንድነው ነውሩና ጥፋቱ?” አሉና አባ አንገታቸውን ደፉ።
“ነውሩና ጥፋቱማ” ብለው እጨጌም አባን ገለማምጠው፡ የችሎቱንም ሁኔታ ቃኝተው ክርክራቸውን ቀጠሉበት። “ነውሩና ጥፋቱማ እንደ አባትነትዎ ከንጉሥዎ አጠገብ ሆነው መምከርና ማስተማር ሲገባዎ በወንጌል ስም፡ በክርስቶስ ስም ከሰው አገር ገብተው ሃይማኖት እየበረዙ ወንድምና ወንድም ለማፋጀት ተንኮል እየሠሩ መገኘትዎ ነው” ብለው ሲመልሱላቸው ችሎቱ “ይበል ይበል” ብሎ አስተጋባላቸው።
አፄ ዮሐንስ አንገታቸውን አቀርቅረው ሲተክዙ ቆዩና በሆዳቸው ውስጥ ሲጤስ የነበረውን ንዴት ደጋግመው በመተንፈስ ካስወጡት በኋላ፤
“እኮ ለዚህስ የሚሰጡት ምላሽ አለዎት?” ብለው ጠየቋቸው የዐይኖቻቸውን ቅንድቦች ዘግተው።
“የንጉሥ ነፍስ አባትነት ከሀገራቸው ወጥታችሁ አታስተምሩ ብሎ አይከለከልም፡ እርሳቸውስ የከዲቡ” ብለው ተናግረው ሳይጨርሱ እጨጌ አቋረጧቸውና፤
“ጃንሆይ! በዚህ ችሎት የምትገኙ መኳንንትና ሊቃውንት! ልብ በሉልኝ! ‘ስሱ ሲበላ ይታነቃል! ሐሰተኛ በአነጋገሩ ይታወቃል እንዲሉ፥ የግብጽን ጦርና የመኳንንት ወስላቶች የምትረዱስ እናንተ አይደላችሁም? እውነተኞቹ የወንጌል ሰባኪዎች ከሆናችሁ ቀደም ሲል የቱርክ ጦር ዛሬም ግብጾች ክርስቲያኑን ሁሉ “እስላም ካልሆንክ” እያሉ ሲያስጨንቁት ለምን አልገላገላችሁም?” ብለው አንገታቸውን አሰገጉባቸው።
“እኮ? የደንከልን የባሕር በርስ ለንግድና ለወታደር ተግባር እንዲውል አሳልፋችሁ አልሰጣችሁም? የትንባሆ ዘርስ በእርሻ ላይ እየዘራችሁ ሕዝቡን እያስለመዳችሁት አይደለም? ለግብጥ ጦርና እኔን ካሎረፉ ወስላቶችስ ጥግና ጋሻ ሁናችሁ የለም? ይህን ሁሉ ታምናላችሁ? ትክዳላችሁ?” ብለው አፄ ዮሐንስም ቁጣና ፍጥጫ ጨመሩበት።
Continue reading…AtseYohannesNegusMenilik2