Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

 • November 2008
  M T W T F S S
   12
  3456789
  10111213141516
  17181920212223
  24252627282930
 • Archives

 • Categories

 • Recent Posts

Ethiopians Should Sacrifice

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on November 22, 2008

sacrifice

በአንድ ዘርፍ፣ በአንድ ግለሰብ፣ በተወሰነ ቡድንና በተወሰነ አጋጣሚ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ብቻ አገር አይቀናም፣ ሕዝብ አይበለፅግም፣ ነፃነትና ሉአላዊነት አይረጋገጥም፡፡ ሁሉም በየሙያውና በየዘርፉ የድርሻውን ሲጫወት እንጂ፡፡

ወታደሩ የአገርን ዳር ድንበርና ሉአላዊነት ለመጠበቅ መስዋዕትነት ይከፍላል፡፡ የድርሻውን ይጫወታል፡፡ የአገር መከላከያ ሰራዊት ብቻ በሚከፍለው መስዋዕትነት ግን አገር አይቆምም፡፡


ምሁሩ እየተመራመረ፣ እየተማረና እያስተማረ አገርን ያሳድጋል፡፡ የመብት፣ የልማት፣ የሰላም መንገድን ያሳያል፡፡ ምሁራዊ ዋጋና መስዋዕትነት ይከፍላል፡፡ በምሁር ብቻ ግን አገር አይቀናም፡፡

መሪዎች ይመራሉ፣ መንገድ ያሳያሉ፣ ያስተባብራሉ፣ ፖሊሲ ይነድፋሉ፡፡ በዚህም ለአገር ያላቸውን ሃላፊነት ያረጋግጣሉ፡፡ መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ በመሪ ብቻ ግን የሚቀና አገር የለም፡፡

ፖሊስ ወንጀልን ይከላከላል፣ ሰላምና መረጋጋትን ይፈጥራል፣ ከወንጀለኞች ጋር ሲዋጋም መስዋዕትነት ይከፍላል፡፡ በፖሊስ ብቻ የሚቀና አገር ግን የለም፡፡

ጋዜጠኛውም መረጃ ይሰበስባል፣ ያሰራጫል፣ ሕዝብ ያሳውቃል፣ ያስተምራል፡፡ አስፈላጊ መስዋዕትነት እየከፈለም አገርን ያሳድጋል፡፡ በጋዜጠኛ ብቻ ግን የሚቀና አገር የለም፡፡

ባለሃብቱም፣ ነጋዴውም ይሰራል፣ ይለፋል፣ ያለማል፣ ሃብት ይፈጥራል፡፡ መስዋዕትነት ይከፍላል፣ አገር ያበለፅጋል፡፡ በባለሃብቱ ብቻ የሚቆም አገር ግን የለም፡፡

ሰርቶ አደሩ ሕዝብም ይለፋል፣ ላቡን ያንጠፈጥፋል፣ ዋጋ ይከፍላል፡፡ አገሩን ያለማል፣ ያበለፅጋል፡፡ በወዝአደሩ ብቻ ግን አገር አይለማም፡፡

አርሶ አደሩ ያመርታል፣ ይመግባል፣ ያለማል፣ ይከላከላል፣ መስዋዕትነት ይከፍላል፣ አገሩን ያሳድጋል፡፡ በአርሶ አደር ብቻ ግን አገር አያድግም፡፡

አርቲስቱም፣ ስፖርተኛውም፣ ዲፕሎማቱም፣ መካኒኩም፣ ፓይለቱም፣ ሾፌሩም ሁሉም በየሙያው በሚያደርገው አስተዋፅኦና በሚከፍለው መስዋዕትነት አገር ያድጋል ይበለፅጋል፡፡ በተወሰነ ዘርፍ ብቻ አገር አያድግም፡፡

ሁሉም በሙያው ይረባረብ፣ አገሩን ያሳድግ፣ ዋጋና መስዋዕትነት ይክፈል፡፡ ያኔ ነው ኢትዮጵያ የበለፀገችና የጠነከረች ጠንካራ የምትሆነው፡፡

በሙያችን አስተዋፅኦ ለማበርከት ሙያችን የሚጠይቀውን እውቀትና ብቃት ዋጋና መስዋዕትነት በሚገባ ጠንቅቀን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ እሰቲ ስለራሳችን ሙያ እናውራ፡፡ መገናኛ ብዙሃን ነን፡፡ ፕሬስ ነን፣ ጋዜጠኞች ነን፣ ሕዝብን የማሳወቅና የማስተማር ኃላፊነት አለብን፡፡

ስናሳውቅና ስናስተምር ግን ሁሉም ይወደናል ማለት አይደለም፡፡ ሕዝብ የማወቅ መብት አለው ብሎ የሚያምን ቀናና ንጹህ ወገን በስራችን ይወደናል፡፡ የጋዜጠኛነት ሙያን ያከብራል፡፡ ለፕሬስ ያለው ምኞትና እንቅስቃሴም “እደጉ፤ ተመንደጉ” የሚል አዎንታዊ መንፈስ ይሆናል፡፡ ግን ደግሞ ከሕዝብ መካከል ማወቅና መማር የማይፈልግ ወገንም አለ፡፡ የማይፈልግ ብቻ ሳይሆን የሚያስተምርና የሚያሳውቅ ጋዜጠኛን ለማጥፋት የሚንቀሳቀስ አለ፡፡ ይህ ማለትም ፕሬስ ወዳጅ እንዳለው ሁሉ ጠላትም አለው ማለት ነው፡፡

የፕሬስ ጠላትነት በሁለት ይፈረጃል፡፡ ጋዜጠኛን በገንዘብ መደለል ፀረ ፕሬስ ነጻነት ነው፡፡ ጋዜጠኛ መረጃ እንዳያገኝ ማድረግም ፀረ ፕሬስ ነፃነት ነው፡፡ ጋዜጠኛን መከፋፈልም እንደዚሁ፡፡

እንደዚህ ዓይነት የፕሬስ ጠላትነት የሚወገዝ ነው፡፡ ሆኖም የሕብረተሰቡ ግንዛቤ ባደገ ቁጥር፣ ጊዜ እየረዘመ ሲሄድ ይፈታል፣ ይወገዳል የሚል ተስፋ ቢኖርም ብዙ መጯጯህ ሊያስከትል ይችላል፡፡

የፕሬስ ጠላትነት ወደ ሃይል፣ ድብደባና ግድያ ሲያመራ ግን የተመረጠው የወንጀል መንገድ ስለሆነ ሊከተል የሚገባው ማውገዝ ብቻ ሳይሆን በሕግ ቁጥጥር ስር ማዋልና ለፍርድ ተገዥ ማድረግም ይጠበቃል፡፡

በቅርቡ በፕሬስ ላይ እየተደረገ ያለው የወንጀል ተግባርም ፍፃሜው ወደ ሕግ ማቅረብና ተገቢ ፍርድ መስጠት ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ ወርዋሪን ብቻ ሳይሆን አስወርዋሪን፣ ተላላኪውን ብቻ ሳይሆን ላኪውን፣ ገንዘብ ተቀባዩን ብቻ ሳይሆን ገንዘብ ከፋዩ ለፍርድ እንደሚቀርቡ እምነታችን ነው፡፡ ከዚህ በላይ ፕሬስ እርካታ አይኖረውም፡፡

ይህ በወንጀለኞች ላይ መፈጸም ያለበት ጉዳይ ሲሆን ራሱ ፕሬስ ግን ተጎዳሁ፣ ተመታሁ ብሎ ለአገር እድገትና ልማት መክፈል ያለበትን መስዋዕትነት ከመክፈል ወደኋላ ማለት የለበትም፡፡

ሁሉም በሙያው መስዋዕትነት ይክፈል ስንል እኛ የዚህ ጋዜጣ ባለድርሻም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ማለታችን ነው፡፡ መታሠር፣ መደብደብ ከመስዋዕትነት ዝግጁነት ወደ ኋላ አያሸሸንም፡፡ በጭራሽ” መፈክራችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለዚህ ደግና ቅን ሕዝብ ያልተሰዋን ለማንስ እንሰዋለን ነው፡፡ በበቂ ሁኔታ ባለመስራታችን በምንከፍለው መስዋዕትነት በጭራሽ ቅር አይለንም፡፡

ይህ ለማንም ፀረ ፕሬስና ለማንም ወንጀለኛ ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ “እንፅፋለን ገና” ብለናል፡፡ መስዋዕትነት እንከፍላለን ገና ማለታችን ነው፡፡ መፈክራችንም ነፃ ፕሬስ! ነፃ ሃሳብ! ነፃ መንፈስ ነው!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: